Deuteronomy 18

የካህናትና የሌዋውያን የመባ ድርሻ

1ሌዋውያን ካህናት፣ የሌዊ ነገድም ሁሉ ከእስራኤል ጋር የመሬት ድርሻ ወይም ርስት አይኖራቸውም፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መባ ይብሉ፤ ድርሻቸው ነውና። 2በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስታቸው ነው።

3ኰርማ ወይም በግ የሚሠዋው ሕዝብ ለካህኑ የሚሰጠው ድርሻ ወርቹን፣ መንገጭላውንና ሆድ ዕቃውን ነው። 4የእህልህን፣ የአዲሱን ወይንህንና የዘይትህን በኵራት እንዲሁም ከበጎችህ በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጕር ትሰጣለህ፤ 5በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም ቆሞ ለዘላለም ያገለግል ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከነገዶችህ ሁሉ እርሱንና ዘሮቹን መርጧል።

6አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከየትኛውም በእስራኤል ካሉት ከተሞችህ መካከል በፍጹም ፈቃድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ቢመጣ፣ 7በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆመው እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ወንድሞቹ፣ እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስም ያገልግል። 8ከቤተ ሰቡ ንብረት ሽያጭ ላይ ገንዘብ ቢቀበል እንኳ፣ ባልንጀሮቹ ከሚያገኙት ጥቅም እኩል ይካፈላል።

አስጸያፊ ድርጊቶች

9አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ፣ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተል። 10በመካከልህ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ
ወይም ወንድ ወይም ሴት ልጁን የሚገድል
ሟርተኛ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገላጭ፣ ጠንቋይ
11ወይም በድግምት የሚጠነቍል፣ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። 12እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ ነውና። ከእነዚህ አስጸያፊ ልምዶች የተነሣም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ያባርራቸዋል። 13በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ነውር አልባ ሁን።

ነቢይ ስለ መነሣቱ

14ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፣ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን ይህን እንድታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አልፈቀደልህም። 15አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱን አድምጥ። 16በኮሬብ ጉባኤ በተደረገበት ዕለት፣ “እንዳልሞት የአምላክህ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ድምፅ አልስማ፤ እንዲህ ያለውንም አስፈሪ እሳት ደግሜ አልይ” ብለህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ያህዌ ኤሎሂም) የጠየቅኸው ይህን ነውና።

17 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “የተናገሩት መልካም ነው፤ 18ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌን በአፉ አደርጋለሁ፤ የማዝዘውንም ሁሉ ይነግራቸዋል። 19ማንም ሰው ነቢዩ በስሜ የሚናገረውን ቃሌን ባይሰማ፣ እኔ ራሴ በተጠያቂነት እይዘዋለሁ። 20ነገር ግን እንዲናገር እኔ ያላዘዝሁትን ቃል በድፍረት በስሜ የሚናገርም ሆነ በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ይገደል።”

21አንተም በልብህ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያልተናገረውን መልእክት እንዴት ማወቅ እንችላለን?” ብትል፣ 22ነቢዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም የተናገረው ካልተፈጸመ ወይም እውነት ሆኖ ካልተገኘ፣ መልእክቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተናገረው አይደለም። ያ ነቢይ በድፍረት ተናግሮታልና እርሱን አትፍራው።

Copyright information for AmhNASV